WE NEED FREEDOM!

WE NEED FREEDOM!

Saturday, April 12, 2014

አዎ ማኅበረ ቅዱሳንን ተጠንቀቁ! ትልቁ ስጋት እሱ ነውና

ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ሰንደቅ ጋዜጣ በሚያዝያ 1/2006 ዓ.ም እትሙ ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ ያወጣው ቃለ መጠይቅና ሀተታ ነው [i] :: ሶስቱም አስተያየት ሰጭዎች “ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ ነው:: ስለዚህም መንግስት ሊያፈርሰው ነው ” የሚለው ወቅታዊ ዜና ምንጩ ከየት እንደሆነ ግልጽ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል :: በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አበበ ወርቁ ጉዳዩን “በሬ ወለደ ነው” ብለው ሲያጣጥሉት ፣ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ደግሞ ” የዚህ ወሬ ምንጩ ከየት እንደሆነ አናውቅም” ሲሉ ተመሳሳይ ነገር ተናግረዋል።
Mahibere Kidusan EOTC
ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንዴ?
በ 1955 እ. ኤ. አ የተመሰረተውና መቀመጫውን በኔዘርላድና በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው Open Doors : Serving Persecuted Christians Worldwide [ii] የተሰኘው ግዙፍ ድርጅት 2013 እ. ኤ. ኣ ባወጣው World Watch List ላይ ክርስትያኖችን በማሰቃየት በ63 ነጥብ ኢትዮጵያ 15ተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝና ፣ ለዚህም ስቃይ ዋና ተዋናይ ከሆኑት አካላት አንዱ ማኅበረ ቅዱሳን እንደሆነ ጽፎ ፣ ሊስቱንም በመላው ዓለም በትኗል [iii] ። ይሄው በመላው ዓለም በድረ ገጽና በተለያዩ ኤለክትሮኒክ ሚድያዎች (hard and soft copy) የተበተነው ሪፖርት ከመስክ የመረጃ ሰራተኞቼ ፣ ከምሁራንና ከሰላዮቼ አገኘሁ ባለው መረጃ መሰረት አቶ መለስ ዜናዊን ሞት ቀደማቸው እንዲ ማኅበረ ቅዱሳንን እንክትክቱን ሊያወጡት አቅደው እንደነበረ ፣ ቀጣዩም ግዜ ማኅበረ ቅዱሳን የሚገንበት ግዜ እንደሚሆንና ይሄም ለተሐድሶዎች አስቸጋሪ ግዜ ስለሚሆን ከማኅበረ ቅዱሳንን እንዲጠበቁ እንዲህ በማለት ያትታል
“The death of Prime Minister Meles Zenawi, who sought to crush Mahibere Kidusan, the fanatical group inside EOC, is considered a big blow for the renewal movements. Zenawi was not a supporter of those movements, but his actions against Mahibere Kidusan for political survival were considered by the EOC renewal movements as helpful for less squeeze. His replacement, Haile Mariam Desalegn, does not possess the political and religious background required to confront the fanatical group. Mahibere Kidusan is currently riding high and…. In addition to this, the death of the EOC leader is a big shock for the renewal movements as he was reluctant to take action against them. “ [iv]
ይሄው ዓለማቀፋዊ “የክርስትያኖች እንባ ጠባቂ” ነኝ የሚለው ድርጅት ማኅበረ ቅዱሳን በመንግስት የደህንነት መዋቅር ውስጥ ዘልቆ እንደገባና የመንግስትን ስልጣን በመቆጣጠር በተለይ “የተሐድሶን ቡድን ” ለማጥፋት መነሳቱን በዚህ መልኩ ሪፖርቱ ላይ ገልጾታል
(MK) normally monitor the churches. The fanatic group inside the EOC (Mahibere Kidusan) has to be mentioned here. Particularly Open Door Field experts report that the group is now a growing threat for non-traditional protestant churches and renewal movements with in the EOC. The group ( MK) allegedly has an ambition to influence and control the government policies to restrict the activities of other religions. There are reports that Mahibere Kidusan has managed to infiltrate the government security and administrative apparatus. In the absence of a powerful leader and the death of a relatively moderate patriarch (late leader of EOC) the next move of the group is nervously watched.[v]
እስካሁም “ያዋጣናል ፤ ማኅበሩን ለመምታት ጥሩ መላ ነው”  ብለው ያሴሩት “ማኅበሩ አስራት ይወስዳል፣ ግብር አይከፍልም ፣ ሕንጻ ገንብቷል ወዘተ” የሚል ነበር። ማኅበሩ አስራት እንደማይወስድ ፣ ሂሳቡንም በተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኦዲት በማስደረጉና ከግብርና መሰል ክፍተቶች የጸዳ መሆኑን በማረጋገጡና የውንጀላ ክፍተት በመጥፋቱ ሌላ ዜማ ጀምረዋል። አሁን ደሞ ክሱ “ማኅበሩ መንግስት ደህንነት መዋቅር ውስጥ ገብቶ ሊያፈርሰን ነው” የሚል ሆኗል።ይሄም እንደማያዋጣ ያወቁት እኩያን አሁን ደሞ የመጨረሻ ጥይታቸው ተቀይሯል። ማኅበሩ ፖላቲካ ውስጥ ገብቷል እና መንግስት ወዮልህ አይነት ዝባዝንኬ።
እናም  ማኅበረ ቅዱሳንን ተጠንቀቁ !
ይሄው ሪፖርት  ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስትያን ውስጥ ገብተው፣ ቤተ ክርስትያንን እየገዘገዙ ላሉ ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው ለሰየሙ ውስጠ ተኩላ ወገኖቹ ያስተላለፈው ጥሪ አንድ ነው :: “አክራሪው ማኅበረ ቅዱሳንን እየበረታና እየጠነከረ ስለሄደ የሚቀጥሉት አመታት ለተሐድሶዎች እጅግ አስቸጋሪ ነውና … ማኅበረ ቅዱሳንን ነቅታችሁ ጠብቁ:: ከዚህም ስጋት የመነጨ ይመስላል ግብረ አበሮቻቸው ማኅበረ ቅዱሳንን ለማወክ ያለ የሌለ ሃይላቸውን አስተባብረው መንጫጫት ከጀመሩ ሰነባተዋል
Now, in his absence and with the government’s reduced leverage, this fanatic group (Mahibere Kidusan) appears to be taking charge. The coming months may bring difficult times for the renewal movements inside the EOC…the next move of the group is nervously watched.[vi]
ይሄ ድርጅት መንደርተኞች የፈጠሩት የሰፈር እቁብ አይደለም:: በመላው ዓለም ኔት ወርክ ያለው መሰረተ ሰፊ ድርጅት ነው:: የሚያወጣቸውንም ሪፖርቶች ሚሊዮኖች ያነቡታል:: የኢትዮጵያ “ክርስትያኖችን ዋይታ” በተመለከተ ያወጣው ጽሁፍ ግን ይገርማል:: ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ክርትስትያኖች ተገድለዋል:: ተሳደዋል:: አብያተ ክርስትያናትም ተቃጥለዋል:: ገዳማትም ተደፍረዋል:: ክርስትና ለሚገደው አካል እነዚህ ብዙ የሚያስጽፉ ነበሩ:: ይሄ ሪፖርት ግን ያተኮረው ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ነው:: የማኅበሩም ወንጀሎች ብሎ ሊነገረን የሚፈልገው አንድ ነገር ” ማኅበረ ቅዱሳንን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንን ትምህርትና ዶግማ አፍርሰው ወደ ሌላ እምነት ድርጅት ለመቀየር የተነሱ ተሐድሶዎችን አላስቀምጥ አለ:: ለተሐድሶ እንቅስቃሴ እንቅፋት ሆነብን “የሚል ነው:: እንግዲህ የማኅበሩ ወንጀል ይሄ ነው:: ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የተናገሩትንም አስተያየት ጠምዝዞ ” ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሞት ቀደማቸው እንጂ ሊያፈራርሱት ነበር” በማለት እውነቱን ሳይሆን ምኞቱን ተርኮልናል:: የሚገርመው ” ማኅበረ ቅዱሳንን በማፍስ ሂደት ጉልህ ሚና አልተጫወቱምና ተተኪው ጠቅላይ ሚኒትር አቶ ኃይለማርያምን “አቅም ያነሳቸው” እስከማለት ደፍሯል:: ፓትርያርክ ጳውሎስንም ” ተሐድሶ ላይ እጃቸውን ማንሳት የማይፈልጉ ለዘብተኛ” ሲል አሞግሷቸዋል:: እንደዚህ ድርጅት ዘገባ ቤተ ክርስትያንን ለመሰርሰር ሰርገው የገቡ መናፍቃን ሰማዕታት ሲሆኑ፣ የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም በሚል ለቤተክርስትያን ትውፊትና እምነት መጠበቅ የሚደክመውን ማኅበረ ቅዱሳንን ደግሞ አሸባሪ ፣አክራሪ የሚል የስም ጥላሸት እንዲቀባ ተደርጓል:: እንግዲህ የማህበረ ቅዱሳን ወንጀሉ ይሄ ነው::
ማኅበረ ቅዱሳን ወሳኝ ሃይል ሆኗል
ከቅርብ ግዜ ወዲህ ማኅበረ ቅዱሳንን በአክራሪነትና በነውጠኛነት የመፈረጁ አባዜ በአካዳሚክ ጽሁፎች ላይም እየታየ ነው :: ለምሳሌ የዶክተር ጥበበ እሸቴን የዶክትሬት ማሟያ ጽሁፍ ማንሳት ይቻላል:: ዶክተር ጥበበ በ 1960ዎቹ ውስጥ በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተሳትፎ የበራቸው እና በኋላ ደግሞ የፕሮቴስታንቱን ዓለም በመቀላቀል በዛው ድርጅት ውስጥ የአስተዳደር ቦታ እስከመያዝ የደረሱ ሰው ናቸው:: እኚህ ሰው 2009 ላይ The Evangelical Movement in Ethiopia : Resistance and Resilience በሚል ርዕስ የጻፉትን የዶክትሬት ሟሟያ ጽሁፋቸውን አሳትመዋል[vii]:: በዚህ አወዛጋቢ መጽሐፍ ዶክተር ጥበበ ማህበረ ቅዱሳንን militant, aggressive, anti evangelical በማለት ጥላሸት በመቀባት አንባቢን የሚያደናግር አንቀጽ አስፍረዋል:: ያይጥ ምስክሯ ድንቢጥ ነው ነገሩ::
The emergence of a highly aggressive and more militant movement that arose with in the Orthodox Church under the name of Mahibere Kidusan in recent years should be seen in multidiscrusive context…     (Mahibere Kidusan) as a nationalistic and strongly anti-evangelical movement enjoying the backing of some orthodox conservative intellectuals and elements of the urban youth , the new religious strain is becoming a significant force [viii]
ዶክተር ጥበበ ለምን ዓላማና በምን መረጃ militant ( ነውጠኛ) anti evangelical (ጸረ ወንጌል) እሰከማለት እንደደረሱ ባላውቅም እሳቸውም ግን ገና በ2009 ማኅበረ ቅዱሳን significant force ሆኖዋልና አስቡበት ሲሉ አስገንዝበው ነበር:: ምንም እንኳን ዶክተር ጥበበ እሸቴ በዚህ ጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ በርካታ አመኔታ የሚጎድላቸው ነጥቦችን ቢያስነብቡንም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ውስጥ፣ ቤተክርትስያኗን ወደ ሌላ እምነት ድርጅት ለመቀየር በስውር የሚሰሩ የተጠናከሩ ህቡዕ ቡድኖች እንዳሉና ተጽኗቸውም በሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ በየማህበራቱ ፣ በየአጥቢያ ቤተክርትያንቱ እንዲሁም ገዳማቱን ሳይቀር መታየት መጀመሩን የውስጥ አዋቂ በሚመስል ሁኔታ እንዲህ በማለት ገልጸውታል::
Today, many underground movements are operating with in Ethiopian Orthodox Church, some with evangelical and others with Pentecostal convictions. ..Some of these movements exemplify attempts at religious innovation, though it is hard to plot their trajectories because of their hidden nature and complex character. Such developments are affecting wide ranging areas of the established structure of the Orthodox institutions, such as Sunday Schools, the mahibers, the monastic centers, and even the local churches in major cities. [ix]
የፕሮቴስታንቱ ዓለም ፓስተሮችም ከ34,000 የማያንሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርትያናት ውስጥ ገብተው ቤተ ክርስትያኗን ወደ ፕሮቴስታንቱ ዓለም ለመገልበጥ አባላትን እየመለመሉና ስልጠና እየሰጡ እንደሆነ በጀብዱ መልክ በአደባባይ እየተናገሩ ነው::
The evangelist is hopeful that the seeds of revival are being planted and nurtured in the estimated 34,000 Orthodox churches in Ethiopia and abroad. So far more than 600 people have successfully completed the two-week course.[x]
አልፎ ተርፎም ማኅበረ ቅዱሳንን ባይኖር የተሐድሶ እንቅስቃሴ ቤተክርትያኗን ሙሉ ለሙሉ ይቆጣጣራት እንደነበር በይፋ እየተጻፉ ነው:: ማኅበረ ቅዱሳንም ላይ ጥርሳቸውን የሚያገጫግጩት ለዚህ እኩይ ዓላማቸው እንቅፋት ስለሆነባቸው ነው ።ለዚህም ዓላማቸው ስኬት ማኅበረ ቅዱሳንን ሊያፈስርና ሊበትን የሚችል ዘርፈ ብዙ ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ:: ቤተ ክህነቱ ውስጥ በገንዘብ የገዟቸው ቅጥረኞቻቸው ማኅበሩን ለማፍረስ የቻሉትን ያህል ሄደዋል::
ግን ከኪሳራ ውጭ ማኅበሩ ላይ ምንም ያመጣው ጉዳት አለመኖሩ ያሳሰባቸው አካላት አሁን ደግሞ ቤተ ክህነቱ ውስጥ ሰግስገው ላስገቧቸው ቅጥረኞቻቸውና በገንዘብ ለገዟቸው ይሁዳዎች የመጨረሻ ትንቅንቅ እንዲያደርጉ እንደላኳቸው በየቀኑ የምናየው ሃቅ እየሆነ ነው::
ዝነኛው ጋዜጠኛ ተመስገን ዘውዴ የማኅበረ ቅዱሳን የመጨረሻዎቹ ቀናት በሚል ርዕስ በቅርቡ ባስነበበን ግሩም ጽሁፍ ላይም የማኅበሩ ተቃዋሚዎች ቤተ ክህነት ውስጥ አዳራሽ ተፈቅዶላቸው ማድረጋቸውንና የአቋም መግለጫ እስከማውጣት መድረሳቸውን እንዲህ ሲል ነበር ያስነበበን
ለመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል የደረሰው በድምፅ የተቀረፀ የውይይቱ ሙሉ ክፍል እንደሚያስረዳው፣ ተሰብሳቢዎቹ ማኅበሩን በተመለከተ ያወጡት የአቋም መግለጫ÷ የማኅበሩና የዋነኛ መሥራቾችና አባላት የባንክ አካውንት፣ቀላልና ከባድ ተሸከርካሪዎች ጨምሮ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች፣ ት/ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት፣ የአክስዮንተቋማት፣ የንዋያተ ቅድሳት ማምረቻዎችና ማከፋፈያዎች፣ ከቀረጥ ነጻ የገቡና በመግባት ላይ ያሉ ዕቃዎችበሚመለከታቸው የመንግሥት መሥ/ቤቶች እንዲታገዱ በቅ/ሲኖዶስ አማካይነት ደብዳቤ እንዲጻፍ፤ ከምእመናንበቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ የሚቀበለው ዓሥራት እየፈረጠመበት ስለኾነ እንዳይቀበል ይከልከል፤ የግቢጉባኤያት(የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) እርሱ በሚቀርፀው ትምህርት እንዳይወሰዱብን በደንብ መሥራት፤ተጠሪነቱ ከዋና ሥራ አስኪያጅነቱ ሥር ወጥቶ በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ውስጥ አንድ ንኡስ ክፍል ይኹንየሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡[xi]
ይሄን የአቋም መግለጫ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የተሰብሳቢዎቹ አንዱና ዋና እቅድ የግቢጉባኤያት(የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትእርሱ በሚቀርፀው ትምህርት እንዳይወሰዱብን በደንብ መሥራት፤ ”የሚል ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ለየግቢ ጉባ ኤያት ቀርጾ ያዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት እና መመርያ መጻሕፍቱ በሙሉ ይታወቃሉ። ቢጋሮቹም ፣ መጻሕፍቱም በሊቃውንቱ ታይተው የተመረመሩና የታረሙ ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ናቸው። እርሱ በሚቀርጸው ትምህርት እንዳይወሰዱብን ማለት ትርጉሙ ምንድነው? ይሄ እንግዲህ እየተካሄደ ያለው ቤተ ክህነት አፍንጫ ና ብብት ስር ነው።
ማኅበረ ቅዱሳን የኔ ነው ! ያንተ ነው!  ያንቺ ነው! የኛ ነው!
ምንም እንኳን ቤተ ክርስትያን ከፈተና ተለይታ ባታውቅም ቅድስት ቤተ ክርስትያናችን አሳሳቢ ፈተና ውስጥ ወድቃለች። ከአውሮፓና አሜሪካ ድረስ ሳይቀር ድርጎ የሚታሰብላቸው ሆድ አምላኪዎች የቤተ ክርስትያንን አባቶችን ክብር በማጉደፍ፣ የቤተ ክርስትያንን ትውፊትና ትምህርት በመገዝገዝ፣ ቤተ ክርስትያንን ወደ መናፍቃኑ ጎራ ለማስረከብ ሌት ተቀን እየሰሩ ይገኛሉ። በተለይም ራሳቸውን ተሐድሶ በሚል የሰየሙ ቡድኖች ቤተ ክርስትያኗን ለማፍረስ ቆርጠው ተነስተዋል። ለዚሁ እኩይ ዓላማቸው መሳካት ማኅበረ ቅዱሳን እንቅፋት ስለሆነባቸው ከምሁር እስከ ተርታው አባል ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ዘመቻ ከፍተዋል። የማኅበሩን ስም ለማጥፋት በርካታ ብሎጎች ሥራ ላይ ውለዋል። ብዙ ብር ወጥቶባቸው መጻሕፍት ታትመዋል።ህሊናቸውንና ሃይማኖታቸውን በብር በሸጡ ይሁዳ የቤተ ክህነት ሰዎችም ማኅበሩን ለመምታት ዘርፈ ብዙ ሙከራ ተደርጓል። አንዱም ማኅበሩን ለማፍረስ አቅም ባይኖረውም።አረቦቹ እንደሚተርቱት ውሾቹ ይጮሃሉ።ግመሉ ግን ይጓዛል።
እኛስ ለሃይማኖታችን የሚገደን ኦርቶክሳውያንስ ምን እያደረግን ነው? ማኅበረ ቅዱሳን የቤተክርስትያን እጅ ነው[xii]። የቤተ ክርስትያን አካል ነው።ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር የሚደረግ ትግል ሁሉ ቤተ ክርስትያንን ለመጣል የሚደረግ ሰይጣናዊ ትግል ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚታወጅ ጦርነት በሙሉ ቤተ ክርትያን ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ።ማኀበረ ቅዱሳንንም ኢላማ ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ዋነኛ ምክንያት፣ ይሄ ትውልድ ስለ ኦርቶክሳዊ ማንነቱ የላቀ ግንዛቤ እንዲኖረው ማስተማሩና ከቤተ ክርስትያን ጎን መቆሙ ነው ። የማኅበረ ቅዱሳን ጥንካሬ የቤተ ክርስትያን ጥንካሬ ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚቀሰሩ ጣቶች በሙሉ ቤተ ክርስትያን ላይ የሚቀሰሩ ጣቶች ናቸው ።ስለዚህ ማኅበሩ ላይ የሚደረጉ ትንኮሳዎች ቤተ ክርስትያን ላይ እይሚደረጉ ትንኮሳዎች ናቸውና እያንዳንዳችን ኦርቶዶክሳውያን ቆመን ማሰብ አለብን አለብን።
ማኅበረ ቅዱሳን ይፈርሳል እንዴ ?
“ማኅበረ ቅዱሳን ይፈርሳል” ብለው ለሚቃዡ ሰዎችም እውነታውን አውቀውት ከወዲሁ እርማቸውን እንዲያወጡ ትንሽ ልበል። ዛሬ እኮ የትኛውም ዓለም ብትሄድ የማኅበረ ቅዱሳን ሴል (Cell)  የሌለበት ክፍለ ዓለም የለም።ኢትዮጵያ ውስጥ እያንዳንዱ ቀበሌ ድረስ ” እምቢ ለቤተክርስትያኔ” የሚሉ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት አሉልህ።ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ እያንዳንዱ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ ለቤተ ክርስትያን ሁለንተናዊ እድገትነቅተው የሚሰሩ የማኅበሩ አባላት አሉ ። የማኅበሩ መመርያ እንደሚያዘው እያንዳንዱ የማኅበር አባል የሰንበት ትምህርት ቤት አባል ነው። የትኛውም ቤተ ክርስትያን ሰበካ ጉባኤ ውስጥ ቤ ክርስትያንን ባላቸው አቅምለማገልገል ቁርጥ አቋም ያላቸው የማኅበሩ አባላት አሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የትኛውም የመንግስትም ሆነ የግል ድርጅት ውስጥ የማኅበሩ አባል የሌለበት የለም ። እያንዳንዱ መስሪያ ቤት ያለ ተቀጣሪ የማኅበረ ቅዱሳን ተጽዕኖና አሻራ የሌለበት የለም ። የማኅበሩ ቋሚ አባል ባይሆን እንኳን የማኅበሩ ግን ሙሉ ደጋፊ ነው ።ወይም በዘመኑ ቋንቋ ስትፍቀው ማኅበረ ቅዱሳናዊ ነውማኅበረ ቅዱሳን በየቀኑ ለቤተክርትስያንን ጉዳይ የሚንገበገብ ፣  የሚያስብ ትውልድ ፈጥሯል።ይህ ትውልድ ማኅበረ ቅዱሳናዊ ነው። ቢመረንም ፤ቢዋጠንም።
ከኢትዮጵያም ውጭ የማኅበሩ ቅርንጫፍ የሌለበት ቦታ የለም። በተለይ በሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ ። ዛሬ ዛሬ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የሚደረጉ የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤያት ከሀገር ውስጡ የማይተናነሱ እየሆኑ ነው። በዓረቡ ዓለምና በዕሥያ ያለው የማኅበሩ እድገትም ቀላል አይደለም። የትኛውም ክፍለ ዓለም ላይ የቤተ ክርስትያን ጉዳይ የሚገደው በቤተ ክርስትያን ጉዳይ ዝም የማይል የማኅበረ ቅዱሳን ሕዋስ አለ። ባጭሩ ማኅበሩ global ሆኗል። ወይ ደግሞ ነፋስ ሆኗል።አትይዘው አትጨብጠው። ነፋስ የማይነፍስበት ቦታ እንደሌለ ሁሉ ማኅበሩ የሌለበት ቦታ የለም።ማን ነበር ማኅበረ ቅዱሳን የሃሳብ መስመር ( Imaginary line) ሆኗል ያለው። ማኅበረ ቅዱሳንን ልዝጋው ብሎ የሚያስብ አላዊ እንኳን ቢመጣ አዲስ አበባና በየዞኑ ያለውን ጽፈት ቤት ሊዘጋ ይችል ይሆናል።ማኅበረ ቅዱሳንን ማጥፋት አይችልም::  ዋናው የማኅበሩ ሥራ የሚሰራው በያንዳንዷ ደብር ፣ በየሰበካ ጉባኤው ፣ በየሰንበት ትቤቱ ፣ በየ አባላቱ ቤት ስለሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚያመጣው ለውጥ insignificant ነው። ሰሜን አሜሪካ ያለው ማዕከል ብቻውን አዲስ አበባ ያለው ማስተባበርያ የሚሰራውን ሥራ የምስራት አቅም አለው። እድሜ ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዛሬ አሜሪካ ሆነህ በያንዳንዱ ቀበሌ ፣በያንዳንዱ አጥቢያ ያለውን አባል ለቤተ ክርስትያን ሥራ ማስተባበር ከባድ አይደለም። It is a click or one call away. ማኅበሩ በአንድ የጸሎት ቋንቋ የሚናገሩ ፣ በአንድ የእምነት ልብ የሚመሩ ፤ እንደ አንድ ቃል ተናገሪ እንደ አንድ ልብ መስካሪ የሆኑ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኦርቶክሳውያን ስብስብ ነውና እንዲህ በቀላሉ እንደ አንቧይ ካብ አትንደውም።ብትሰረስረውም መሰረቱ ጠንካራ አለት ነውና አታፈርሰውም። ከሁሉም በላይ የማኅበሩ ጠባቂ እመብርሃን ናትና ገና ይሄ ማኅበር ያድጋል። ይሰፋል።http://ecadforum.com/

Thursday, April 10, 2014

ከአገር መውጣት የማይችሉ ባለሥልጣናት በጭንቀት ውስጥ ናቸው

"አሁን ያለው ኢህአዴግ ላዩ በቀለም ቀቢ የተዋበ ይመስላል"
stressed


ኢህአዴግ በሙስና ስም የ”ማጥራት ዘመቻ” ማካሄዱን ተከትሎ የተከሰተው አለመተማመንና እርስ በርስ በጥርጥር የመተያየት ችግር ካድሬውን ማስጨነቁ ተጠቆመ። ኢህአዴግን ለመሰናበት የሚፈልጉ በርካታ ካድሬዎች “ለምን” በሚል የሚቀርብላቸውን ጥያቄ በመፍራት የግድ ፓርቲውን መስለው እንደሚኖሩ ተገለጸ።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ቀደም ሲል ኢህአዴግን ተሰናብተው የወጡና በተለያዩ የውጪ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው በማገልገል ላይ ካሉ ያገኘውን መረጃ በመጥቀስ እንደዘገበው፣ የቀድሞ የትግል ጓደኞቻቸው “በደህና ጊዜ ተገላገልክ” በሚል በፓርቲው ውስጥ ችግር ስለመኖሩ እየነገሯቸው ነው። አብዛኞቹ ኢህአዴግን ተለይተው በሰላም ስለመኖር እንደሚያስቡ ነው የተሰማው።
የቤተሰቦቻቸው የወደፊት እድልና የነሱ በፍርሃትና በጭንቀት መኖር አሳዛኝ እንደሆነ የነገሩት የቀድሞ የኢህአዴግ ሰዎች “አሁን ያለው ኢህአዴግ በቀለም ቀቢ የተዋበ ይመስላል” በማለት አንድ በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ እያገለገለ ያለ የቀድሞ ጓደኛቸው እንደነገራቸው ገልጸዋል።
ለስራ እንኳን ካገር መውጣት የማይችሉ ባለስልጣኖች እንዳሉ ዘጋቢያችን አመልክቷል። በተቀመጡበት ሃላፊነት ወደ ውጪ የሚያስኬድ አጋጣሚ ሲኖር የሚከለከሉ እንዳሉም ያገኛቸውን መረጃዎች ጠቅሶ ዘግቧል። ለሃላፊዎቹ ደህንነት ሲባል የሚሰሩበትን ተቋምና ስም መናገር እንደማይችሉ በመጥቀስ መረጃውን የሰጡት ክፍሎች “ባለስልጣኖቹ በመካከላቸው እርስ በርስ መተማማን ስለማይችሉ ችግራቸውን መወያየት እንኳን አይችሉም” ብለዋል፡፡
“በጣም የሚቀርቡኝ ጓደኞቼ ገንዘብ ወደ ውጪ እንድወስድላቸው እስከመጠየቅ ደርሰዋል” ሲሉ የገለጹት የቀድሞ የኢህአዴግ ባለስልጣን፣ ፓርቲው በሙስና ስም ያካሄደው የሽግግር ወቅት የማጥራት ርምጃ የፈጠረው ስሜት አሁን ድረስ እንዳለ ጠቁመዋል።
ሰሞኑንን ወደ አሜሪካ ያቀኑ የቀድሞ የኢህአዴግ ሰው በማግኘት ተመሳሳይ መረጃ ያሰባሰበው ዘጋቢያችን “ኢህአዴግ በከፍተኛ የመበስበስ አደጋ ውስጥ ይገኛል። በዚህም የተነሳ ካድሬው ተዥጎርጉሯል” ሲል ሪፖርት አድርጓል። ኢህአዴግ በውስጥ ያለበትን ችግር ለማድበስበስ የአባይ ግድብ ላይ ትኩረት በመስጠት “የንቅናቄ ሃይል” በማስፋፋት ላይ እንደሆነም ጠቁሟል።
ድፍን ህዝብ የአባይ ግድብን አስመልክቶ ያለው ስሜት በበጎ መልኩ የሚታይ በመሆኑ ኢህአዴግ ይህንኑ የህዝብ ስሜት ለቅስቀሳና ለበሽታው መደበቂያ ለማድረግ እየተጠቀመበት እንደሆነ ተጠቁሟል። የህጻናት ፕሮግራሞች ሳይቀሩ አባይ ላይ ያነጣጠሩ ቅስቀሳዎች እያስተላለፉ መሆናቸውን ያመለከቱት ሰው፣ “ስለ አባይ ግድብ የሚባለውና የሚሰራው ፕሮግራም ችግር የለውም። በአግባቡ ቢሰራበት ብሔራዊ ስሜት ሊገነባበትም በተቻለ ነበር። ይሁን እንጂ ዓለማው የችግር ማለባበሻ እንዲሆን መደረጉ ነው” ብለዋል።
“መለስ ኢትዮጵያን ቢወድ ኖሮ ከባድመ ጦርነት በኋላ የፈረሰውን ብሔራዊ አንድነትና መግባባት መልሶ መትከል ይቻል ነበር” በማለት የተናገሩት እኚሁ ሰው “በወቅቱ ይህንን ሃሳብ ያነሱ ሰዎች ነበሩ” ሲሉ ቁጭታቸውን ይሰነዝራሉ። በማያያዝም ኢህአዴግ የአባይን ግድብ ተንተርሶ ብሔራዊ አንድነት የሚገነባበት፣ መቀራረብና በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር ብሔራዊ መግባባት የሚደረስበት፣ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ መሰረት የሚጣልበት ቢያደርገው እውነተኛው የኢትዮጵያ ህዳሴ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም ለመተካት ህዋሀቶች የሚያደርጉት ሽርጉድ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ሪፖርት መቅረቡ ተሰምቷል። ይኽው ሪፖርት የቀረበላቸው ክፍሎች ቀደም ሲል እንዳደረጉት የህወሃትን ከፍተኛ አመራሮች በማነጋገር ስህተት እንዳይሰሩ እየወተወቱ ነው።http://www.goolgule.com

Saturday, April 5, 2014

ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ!

መጠላለፍ ወደየትኛው ገደል እየመራን ነው?
fire1

የአዲስ አበባን መኪናዎች በተለይም በጫት የሚሽከረከሩት ታክሲዎችን በማንኛውም መስቀልኛ መንገድ ላይ ለአምስት ደቂቃ ቆሞ የተመለከተ ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው “እኔ ካላለፍሁ ማንም አያልፍም!” በሚል መመሪያ መኪናዎቹ ተቆላልፈው እንዲቆሙ ማድረግ ነው፤ እንደሚመስለኝ የአባቶቻችንን ዕዳ እየከፈልን ነው፤ ዱሮ በደጉ ዘመን ሁለት ኢትዮጵያውያን መስቀልኛ መንገድ ላይ ሲገናኙ አንተ-እለፍ አንተ-እለፍ እየተባባሉ የሰማዕታቱንና የቅዱሳኑን ስም እየጠሩ ይገባበዙ ነበር! ይህ ባህል በጠንካራ የሥልጣኔ ላጲስ ተደምስሶ ጠፍቶ በምትኩ እኔ ካላለፍሁ ማንም አያልፍም መንገዱን ሁሉ መቆላለፍ አዲስ የመጠላለፍ ባህል እየተተከለ ነው፤ የመጠላለፍ ባህል የሚታየው በባቡር መንገዶች ላይ ብቻ አይደለም፤ በብዙ ነገር መጠላለፍ ባህል እየሆነ ነው! የዚህ ዝንባሌ መጨረሻው አሸናፊ የሌለበት ሙሉ ጥፋት ነው።
በመንገዶች ላይ ጥቂት በጫት የሚነዱ መኪናዎች በመቶ የሚቆጠሩ መኪናዎች እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ ይችላሉ፤ ሲያደርጉም በየቀኑ እየታየ ነው፤ በማኅበረሰባዊና በፖሊቲካ ግንኙነትም አንድ ሰው የሚዘራው መርዝ የጊዜው ሁኔታ በሚፈቅድለት ፍጥነት የማኅበረሰቡን አባላት ያዳርሳል፤ እንቆቅልሹ እንደሚለው ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ! ማለት መርዝ፣ እሳት፣ ተላላፊ በሽታ በሕዝቡ ላይ ማሰራጨት ከአምስትና ከአሥር ዓመታት በኋላ ውጤቱ ምን እንደሚሆን መገመት አያቅትም።
ድብብቆሽ አይጠቅምም፤ሁለት ነገሮችን በግልጽ ማውጣት አለብን፤አንደኛ በአሜሪካና በአውሮፓ መሽጎ ፍርሃቱንና ሽቁጥቁጥነቱን ለመሸሸግ መርዙን በኢትዮጵያውያን ላይ የሚረጨው ለምንድን ነው? አገዛዙ ይህንን የሚያደርግበት ምክንያት ግልጽ ነው፤ ከፋፍሎ የመግዛት ዘዴ ነው፤ ከአገዛዙ ጋር በሚደረግ ትግል ከታች ሆነው ከሥልጣን ውጭ የሆኑ ዜጎች በሥልጣን ላይ ከተቀመጡት ጋር እየተቆራቆዙና እየተጋጩ ናቸው፤ ይህንን እኔ የላይና-የታች ግጭት (vertical conflict) የምለው ነው፤ ከወያኔ/ኢሕአዴግ ጋር የሚደረገው ትግል ይህ ነው፤ ይህንን ለማክሸፍ ወያኔ/ኢሕአዴግ ትግሉን ከላይና-ታች አውጥቶ ወደጎን-ለጎን ግጭት (horizontal conflict) ሊለውጠው ይፈልጋል፤ ከወያኔ/ኢሕአዴግም ውጭ በጎሠኛነትና በሃይማኖት አክራሪነት የደነዘዙ ሰዎችም ትግሉን ጎን-ለጎን ሊያደርጉት እየሞከሩ ናቸው።
የፖሊቲካ ትግልን የሚመሩ ሰዎች በጎሠኛነትና በሃይማኖት አክራሪነት ስሜት እየተሳቡ ትግሉን የላይና-የታችነቱን ጠብቀው በተደራቢነት የጎን-ለጎን ትግሉን ይጨምሩበታል፤ ይህ ሲሆን ሀሳብ፣ ጉልበትና ሀብት ይከፋፈላል፤ ይበታተናል፤ ወደዓላማ ለመድረስም ያስቸግራል፤ ወያኔ ወደመጨረሻው ላይ ኢሕአዴግ ብሎ የሰየመውን ቀፎ አስቲፈጥር ድረስ በስሙ ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያነሣ ነገር አልነበረውም፤ ወያኔን ለድል ያበቃው የማታለያ ስሙ እንደሆነ በበኩሌ አልጠራጠርም፤ ከሃያ ሁለት ዓመታት የጎሣ ሥርዓት በኋላ ኢትዮጵያ ቆስላለች እንጂ አልሞተችም፤ የአሐዝ ማስረጃ ለማቅረብ ባልችልም በብዙ ጎሣዎች መሀከል ጋብቻ እንደዱሮው እየቀጠለ ነው፤ ይህንን የቆየ የዝምድና ሰንሰለት ለመበጠስ የሚጥሩም አሉ።
ኒው ዮርክ ተቀምጦ ትኩስ ውሻ (ሆት ዶግ!) እየበላ ለእስላም ኦሮሞዎች የመገዳደያ መመሪያ የሚሰጥ ሰው የመንፈስ ጤንነቱን እጠራጠራለሁ፤ ይህንን የኒው ዮርክ ቀረርቶ ተከትሎ ሌላ የመጠላለፍ አዋጅ ሰማን፤ ቴዎድሮስ ካሣሁን ለአጼ ምኒልክ ስለዘፈነ ከበዴሌ ቢራ ፋብሪካ ጋር ለማስታወቂያ የገባው ውል ሥራ ላይ ከዋለ የበዴሌን ቢራ አንጠጣም ተባለና ማስታወቂያው ተሰረዘ ይመስለኛል፤ ማን እንዳሸነፈ ወደፊት ጊዜ ይነግረናል፤ አሁን ደግሞ ሌላ ማዘዣ ሰማሁ፤ “የስ” በሚለው ውሀ ጠርሙስ ላይ እንስራ የተሸከመችው ኮረዳ መስቀል አድርጋ ነበር፤ ልጅቱ ከነመስቀልዋ የምትታይበትን ውሀ እስላሞች አንገዛም ስላሉ ነጋዴዎቹ መስቀሉን አወለቁባት! ይህንን ማዘዣ ላወጣው አክራሪ እስላም ወረባቦ ቅዳሜ ገበያ ሄዶ እንዲጎበኝ አሳስበዋለሁ፤ ዛሬ ተለውጦ እንደሆነ አላውቅም እንጂ እኔ ብዙ ጊዜ ተመላልሼ እንዳየሁት የወረባቦ ኮረዶች ሁሉ ትልልቅ መስቀል በአንገታቸው ላይ ይታይ ነበር፤ መስቀል የእምነት መግለጫ ይሆናል፤ አያጠራጥርም፤ ግን መስቀል ጌጥም ይሆናል! መስቀል የናዚ ምልክትም ሆኖ ነበር! ለማናቸውም የዚህ ዓይነቱን መጠላለፊያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገምዱ ሰዎች ዓላማቸው ማንንም ለመጥቀም ሳይሆን ፍቅርንና ሰላምን ለማደፍረስ ነው፤ የኢየሱስ ክርስቶስ መሠረታዊ ትምህርት ክፉን በክፉ አትመልሱ ነውና ለተበጠሰው መስቀል አጸፋውን ለመመለስ ማሰብ አይገባም።
ከኒው ዮርክ የተሰማው ቀረርቶም ሆነ የመስቀል ማስወለቁ ጉዳይ የተከሰተበትን ጊዜ ልብ ልንለው ይገባል፤ እስላሞች ስለነጻነት የሚያደርጉት ንቅናቄ በጣም እየጋለ በመሄድ ላይ እያለ ክርስቲያኖችም የዜግነት ግዳጃቸው አድርገውት ድጋፋቸውን በሚሰጡበት ጊዜ ነበር፤ ይህ መሆኑ ጥርጣሬን ይጋብዛል፤ የገጠመውን የእስላሞችና የክርስቲያኖች ሰልፍ በማደፍረስ ወይም በመክፈል የሚጠቀም ማን ነው? የሚጎዳውስ ማን ነው? ሁሉም የትግል አጋፋሪዎች ለዚህ ጉዳይ የሚያስፈልገውን ክብደት ቢሰጡት ትግሉ በጎን-ለጎን እንዳይሄድና እንዳይዳከም ይረዳል፤ ከዚያም በላይ አክራሪነት የሚባለውና የሚያስከትለውም ሽብርተኛነት የሚመጣው እንዲህ እያለ ነው፤ እግዚአብሔር ከዚያ ያውጣን!http://www.goolgule.com

Thursday, April 3, 2014

ኢህአዴግ የአፍሪካ ቀንድ ስጋት?

አሜሪካ መለስ ከቆፈሩት ጉድጓድ ለመውጣት ወስናለች
eprdf and the usa


ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ብቸኛ ተዋናይና ፊት አውራሪ አድርጎ ራሱን የሾመው ኢህአዴግ ለቀጠናው ስጋት እንደሚሆን ተጠቆመ። አልሸባብንና አልቃይዳን ከምንጩ እናጠፋለን በሚል ስትራቴጂ መለስ ከቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥ ሰምጣ የነበረችው አሜሪካ ከጉድጓዱ ለመውጣት ወስናለች። ኢትዮጵያዊያን የሚያምኑትና የሚቀበሉትን መሪ በድፍረት አደባባይ የማውጣት ሃላፊነቱ “አገር ወዳድ” በሚሉ ዜጎችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጫንቃ ላይ ነው።
ህወሃት ያቋቋማቸው ጥቃቅን መንግስታት ከህዝብ ይልቅ ለህወሃት የወደፊት እቅድ ታማኝ በመሆን መጓዛቸው ከቀን ወደቅን የፈጠረው ስሜት ኢህአዴግን እየበላው እንደሆነ የጠቆሙ የዜናው ምንጮች፣ ኢህአዴግ የምስራቅ አፍሪቃ የሰላም አባት ሊሆን ቀርቶ የራሱንም ችግር መፍታት ወደማይችልበት የቁርሾ ማሳ ውስጥ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ህወሃት “በነጻ አውጪነት” ያሰላውና፣ ይህንኑ ዓላማውን በፈለገበት ቀን ተግባራዊ ለማድረግ ያመቸው ዘንድ በየክልሉ ለጣጥፎ ያቋቋማቸውን ፓርቲዎች ሲመሩ የነበሩት አቶ መለስ በድንገት ካለፉ በኋላ ኢህአዴግ ውስጣዊ ሰላሙ መናጋቱ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው። ኢህአዴግ በበኩሉ “የጓድ መለስን ውርስና ራዕይ ያለማዛነፍ እናስቀጥላለን” እያለ አገሪቱን በደቦ እንድተመራ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
አቶ መለስ በጓዶቻቸው ቋንቋ “ተሰው” ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ምክትል ጠ/ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ለመተካት ተቸግሮ ነበር። ደህንነቱን፣ መከላከያውን፣ ፖሊስና ዋንኛ የአገሪቱን ተቋማት ጠቅልሎ የያዘው ህወሃት በቀጥታ አሜሪካ ባደረገችው ጫና ሳይወድ በግዱ አቶ ሃይለማርያምን በጠ/ሚኒስትርነት ለመሰየም ተገደደ። የስልጣን ክፍተቱን በተመለከተ አቻ ድርጅቶችና ህወሃት ውስጥ አለመግባባት ተፈጥሮ ስለነበር “ምደባ” በሚል ኢትዮጵያ በደቦ የሚመሯት አራት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተሰየሙላት።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የአሜሪካ ዲፕሎማት እንዳሉት አሜሪካ ስጋት የገባት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነበር። መለስ እንዳለፉ ልዩ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ በመላክ ሁኔታውን በመገምገም ስራ የጀመረችው አሜሪካ አሁን አሁን በህወሃት ስትራቴጂ የተሰራው ኢህአዴግ የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ዋንኛ የችግር ምንጭ ስለመሆኑ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። በዚህም የተነሳ የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየመከሩበትና የመፍትሔ ስትራቴጂ እየነደፉ ነው።
“We cannot afford to lose Ethiopia” አሜሪካ ኢትዮጵያን ልታጣት አይገባም በማለት ለጎልጉል የዋሽንግቶን ዘጋቢ የተናገሩት የዲፕሎማት ምንጭ “የአሜሪካን ባለስልጣናት ኢህአዴግን በተመለከተ የሚጠቀሙት ቃልና የድምጻቸው ቃና ተቀይሯል” ሲሉ የጉዳዩን ክብደት አመላክተዋል።
በዋሽንግቶን የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የምክር ቤት አባላት እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ኢህአዴግን አስመልክቶ ተደጋጋሚ ስብሰባ መቀመጣቸው ታውቋል። አዲስ አበባም ተወካይ በመላክ ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር በግል እየተነጋገሩ ነው። በያዝነው ሳምንትም ለተመሳሳይ ስራ አዲስ አበባ የተጓዙ አሉ። እንደ ዲፕሎማቱ ገለጻ የህወሃት ሰዎች ውስጣዊ ችግር እንዳለ አይቀበሉም። በግል ያነጋገሯቸው የሌሎች ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ግን ኢህአዴግ ውስጡ አለመረጋጋትና ስጋት የተሞላው ስለመሆኑ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ አንድ ችግር ቢፈጠር ለማረጋጋት አስቸጋሪ እንደሚሆን፣ ህዝቡ በተለይ በህወሃቶች ላይ የሚያሳየው ጥላቻ እየተካረረ መምጣቱ፣ በአገሪቱ የሚፈጸመው ያልተመጣጠነ የሃብት ስርጭት፣ አፈናውና ሌሎች የህወሃት/ኢህአዴግ ተግባራት ተዳምረው ህዝቡን ክፉኛ ማስቀየሙ ያልታሰበ ችግር ሊቀሰቅስ እንደሚችል አሜሪካ መገንዘቧን ያወሱት ዲፕሎማት፣ “ህወሀቶች የቀጠናው የሰላም ምንጮች ስለመሆናቸው ለራሳቸው ምስክርነት ለመስጠት ቢሞክሩም በተግባር የሚታየው ግልባጩ ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ላይ የተተከለው የጎሳ አገዛዝ እንደሆነ ያመለከቱት እኚሁ ዲፕሎማት “በጎሳ አስተሳሰብ የተዋቀረው ኢህአዴግ ችግሩ ከገነፈለ ሊቆጣጠረው የሚችል ባለስልጣንና መሪ የለውም። አስተዳዳራዊ ማዕከላዊነት አይታይበትም። በግል የሚወስን ባለስልጣንና ርምጃ የሚወስድ አካል የለውም” ሲሉ የስጋቱን ግዝፈት ያሳያሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ችግሩ ቢከሰት ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰቡ አዳጋች እንደማይሆን ይጠቁማሉ። አያይዘውም “አሜሪካ ቸል ብላ ስትመለከተው የነበረውን ጉዳይ አጽንኦት ብትሰጠው አይገርምም” ብለዋል። አሜሪካ ይህንን የምታደርገው ለራሷ ስትል እንደሆነ ያልሸሸጉት ዲፕሎማት አንድ ጥያቄም ጠይቀዋል። “እናንተስ ለራሳችሁ ስትሉ ምን እየሰራችሁ ነው?” ከረጅም ፈገግታ ጋር።
አልቃይዳን ከምንጩ ማድረቅ በሚለው የመለስ ስትራቴጂ ለኢህአዴግ ግብር ስታስገባ የነበረችው አሜሪካ ግብሯን ስትገብር የኖረችው በፔንታጎን ወታደራዊ ውሳኔ መሰረት ነበር። ኢህአዴግም ግብሩ እንዳይቆምበት በአዲስ አበባ ታክሲ ላይና ህዝብ በሚያዘወትርባቸው ቦታዎች ፈንጂ በማፈንዳት ሲጫወተው የነበረውን ድራማ ዊኪሊክስ (ሹልክ ዓምድ) አምባሳደር ያማማቶን ጠቅሶ ማጋለጡ አይዘነጋም። በዚሁ መነሻ ይመስላል ኢህአዴግ የቀድሞውን ጨዋታ የመጫወት እድሉ እንዳከተመ እንደራሴ ክሪስ ስሚዝ ባደባባይ የመለስን ስብዕና በመዝለፍ ባልተለመደ መልኩ ተናግረው ነበር።
ለጎልጉል መረጃ የሰጡት ዲፕሎማት “እናንተስ” በሚል ለሰነዘሩት ጥያቄ ማብራሪያ ተጠይቀው “እኔ ኢትዮጵያዊ ብሆን አገሬን አስቀድማለሁ” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል። አሜሪካ አማራጭ ማጣቷንም እንደ አንድ ችግር አንስተዋል።
በዲፕሎማቱ አስተያየት ላይ ገለልተኛ ወገኖችን አነጋግረናል። ያሰባሰባንቸው አስተያየቶች “አሜሪካ እዚህ ደረጃ ከደረሰች፣ ኢህአዴግም በዚህ ደረጃ ከተመደበ ተቃዋሚዎች የግል ጉዳያቸውንና ፕሮግራማቸውን ለህዝብ ውሳኔ በመተው ለመጪው ትውልድና ለአገር ሲሉ ከመቧደን በሽታ ሊፈወሱ ይገባል” የሚል ይገኝበታል።
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቀናጅቶ መበተን፣ ተደራጅቶ መፍረክረክ፣ ተደላድለው መስለል በተለያዩ ወቅቶች ህዝብ ተስፋ እንዲቆርጥ አድርገዋል። የሚፎካከሩትን ፓርቲ ትተው እርስ በርሳቸው ለተራ ጉዳይ ሲሻኮቱ ዓመታት አሳልፈዋል። በዚህም የተነሳ “አማራጭ የለም” በሚል ኢህአዴግን ማንገስ ግድ እንደሆነ የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎች “የተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህንን አስተሳሰብ ሰብረው አገር መምራት እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ህብረት መፍጠር ይገባቸዋል። ይህም ካልሆነ የርስ በርስ ውዝግባቸውን ማቆምና የራሳቸውን የቤት ስራ መስራት ላይ ማተኮር ግዳጃቸው ይሆናል” ብለዋል።
ምሁራን ከተደበቁበት ሊወጡ እንደሚገቡም ያሳሰቡ አሉ። አገር የመምራት፣ በህዝብ የመታመን፣ የህዝብን ይሁንታ ማግኘት እንችላለን የሚሉ ከፊት ለፊት፣ አሁን ከፊት ያለውን ችግር በመጥረግ የወደፊቷን ኢትዮጵያ በመገንባትና መጪውን ትውልድ በማዳኑ ስራ አጋዥ ሃይል ለመሆን መወሰን እንደሚገባቸው በመግለጽ ጥሪ አቅርበዋል። ከሁሉም በላይ ግን “አሁን ካለው ህዝብን ካገለለ ዘመናዊ የመሳፍንት ስርዓት ኢትዮጵያንና ህዝቧን ማሻገር የሚችል ሞገሰ ሙሉ፣ ቅን፣ ከጥላቻ የጸዳ፣ ከሥልጣን ይልቅ የወደፊቷን ኢትዮጵያ አሻግሮ መመልከት የሚችል መሪ ወደ ፊት ወጥቶ በግልጽ ለህዝብ የሚተዋወቅበትን መንገድ የማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ድረገጾች፣ ሬዲዮኖች አገር ወዳድ የመገናኛ አውታሮች አጀንዳ አድርገው ሊወያዩበት ይገባል” የሚለው አስተያየት ሚዛኑን የደፋ ሆኗል።http://www.goolgule.com